ርዕይ
ቤተ ክርስቲያን እንደ እምነት ተቋምነቷ በቤተ ክህነቱና በፖለቲካው ስርዓት ውስጥ ጥቅሟ ተጠብቆ፤ እሴቶቿ፤ እምነቷና ትውፌቷ ተከብሮ እንድትኖር፤ ምዕመኖቿም በየትኛውም የሀገሪቷ ክፍል ተዘዋውረው መኖርና ማምለክ የዜግነት መብታቸው መሆኑ ታውቆና በአሁን ወቅት በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያን ልጆቿ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እና መፈናቀል ቆሞ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን ሁለንተናዊ ሰላም ተረጋግጦ ማየት ነው።
አስፈላጊነት
በኦርቶዶክሳዊያን ላይ የሚደርሰው ተደጋጋሚ ጥቃት እና ኢፍትሃዊነት እየጨመረ መምጣቱና መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ እያገኘ በመምጣቱና በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሃሰት ትርክቶቸን በማንሳት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን በረቀቀና በተጠና ስልት አጽድቶ ህልውናዋን ለማጥፋትና ልጆቿን ለመበተን በአንዳንድ የብሔረሰብ እና የፖለቲካ ክፍሎች የሚደረገውን ስውርና ግልጽ ደባ የኦርቶዶክስ ማህበረሰቡ በሚገባ በመረዳት አንድነቱን አጥንክሮ ለሃይማኖቱና ለቤተ ክርስቲያኑ መከታ የሚሆንበትን ንቃት ከፍ በማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት መፈጠር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ ይህንን አገልግግሎት አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡
የጥምረቱ አቋምና አሠራር
ይህ ጥምረት የበጎ ፈቃደኞች ምእመናን ስብስብ ሆኖ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት እና ቀኖና አክብረው ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት መሻሻል እና የምእመናን ደኅንነት ጉዳይ ላይ ለማገዝ የበኩላቸውን ከሚወጡ አካላት ሁሉ ጋር ተባብሮ ይሠራል። ሆኖም ግን በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ እንጂ የየትኛውም ማኅበር ወይም ተቋም ተቀጥላ አይደለም። ይንን አቋም የሚወስድበት ምክንያትም በገለልተኛነትና በነጻነት ተንቀሳቅሶ ማእከላዊ በሆነ መንገድ ሁሉንም ለማገልገል እንዲያስችለው ነው።
ዓላማ
ዓለምአቀፍ ጥምረት በዋናነት የሚከተሉት ላይ ትኩረት አደርጎ ይሰራል፡፡
የምእመናን ደህንነትና አንድነት በዘላቂነት ለማስጠበቅና በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናኖቿ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከትና ወደፊትም እስካሁን የታየው ዓይነት ጥፋት እንዳይከሰት ለመከላከል የሚያስቸሉ ተግባራት ላይ ትኩረት አደረጎ ይሰራል።
የቤተ ክርስቲያን ሰላምና እድገት ሊያረጋገጡ የሚችሉ ተግባራት ላይ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላትን በማስተባበር በጋራ መስራት።
የሃይማኖት መጠበቅና መከበር እንዲረጋገጥ በተለያዩ ፍላጎት ባላቸው አካላት የሚነሱ የሃሰት ትረክቶችንና ክሶችን በመለየት እውቀትን መሰረት ያደረገ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለማስቻል ምሁራንን በማሰባብሰብና መድረኮች በማዘጋጀት በሃሳብ እንዲሞግቱ ያደርጋል፡፡