ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ ቤት
አዲስ አበባ: ኢትዮጵያ
ጉዳዩ:- ቅዱስ ሲኖዶስ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን በተመለከት ያስተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ከፍተኛ ስጋት እንዳለን ስለመግለጽ
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጥምረት የዘንድሮውን የግንቦት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከምንዜውም በተለየ ሁኔታ በንቃት ስንከታተል ቆይተናል፡፡ ጉባኤው ከአጀማምሩ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በግልጽ የተንጸባረቀበት፡ ወከባ የበዛበት እና ለቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ ይቅርና በዓለም ከሚካሄዱ ስብሰባዎች በባሰ ሁኔታ ግርግር የበዛበት ሆኖ መካሄዱ ሂደቱን በቅርበት የሚከታተሉ የቤተ ክርስቲያናችንን ካህናትና ምዕመናንን ያስጭነቀ እና ያሳዘነ ተግባር ሆኖ አልፏል፡፡ በዚሀ ግርግር መካከል በተካሄደው ጉባኤ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን በተመለከተ ተደረሰበት የተባለው ውሳኔ ብዙ ክፍተት የታየበት እና የቤተ ክርስቲያንን የወደፊት ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር በመሆኑ በእጅጉ አሳዝኖናል። ስለሆነም ከታች የተዘርሩትን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በቅንነት በመመልከት እና ከእግዚአብሔር የተሰጣችሁን የእረኝነት አደራ በአግባቡ በመወጣት ቤተ ክርስቲያንን ለመጪው ትውልድ የሚያሻግር ስራ ሰርታችሁ እንድታልፉ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡
1ኛ) በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነው ውሳኔ በተጓደሉ ሀገረ ስብከቶች ላይ በሁለት ዙር ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም መሆኑ አግባብነት ያለው ቢመስልም በአንዳንድ አካላት የብሔር ተዋጽኦ ያለበት በሚመስል መልኩ የሚነገረው አገላለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠው መግለጫ ላይ ታርሞ የማይቀርብ ከሆነ አባቶቻችንን የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርጋችሁና ከምንም በላይ ለቤተ ክርስቲኗ በቀላሉ የማይፈታ ችግር ጥሎ የሚያልፍ መሆኑ እናስገነዝባለን።
2ኛ) የምርጫውም ሂደት የቤተ ክርስቲያኗን ሕግ እና ሥርዓት በመከተል ብቻ እንዲከናወን ለዚህም፤
ሀ) ለተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ መመሪያ እንዲሆን በቋሚ ሲኖዶስ በተሰየመ ኮሚቴ የተጠናው "የኤጲስ ቆጶሳት አመራረጥ መመሪያ" አስመራጭ ኮሚቴው ተግባሩን ከመጀመሩ በፊት በቋሚ ሲኖዶስ እንዲጸድቅ በውሳኔው ላይ እንዲካተት እንጠይቃለን።
ለ) የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በሚያዘው መሠረት በአስመራጭ ኮሚቴነት ከተሰየሙት አባቶች በተጨማሪ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን: ከማኅበራት እና ከምእመናን ተወካዮች በአስመራጭ ኮሚቴ አባልነት እንዲካተቱ እንጠይቃለን።
ሐ) የምርጫው ሥርዓት፡ የቤተ ክርስቲያንን ሀዋርያዊ ተልእኮ ለማስፋፋት ብቻ ያለመ፡ ግልጽ እና ለትችት ያልተጋለጠ እንዲሆን እንጠይቃልን።
3ኛ) ህግና ሥርዓት ጠብቀው ስለ ቤተክርስትያናቸው የሞገቱ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ የመሰከሩ ያለ አግባብ ታስረዋል፤ ታፍነዋል። ስለሆነም መንግስት በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እዲፈታቸው እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ድምጽ የሆኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና ሊሎች የመገናኛ ብዙሃን ላይ የጣለውን አስነዋሪ እግድ እንዲያነሳ በመግለጫችሁ አካታችሁ እንድትጠይቁ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅ
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጥምረት